"ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት'' 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ተከበረ
Description
"ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት''
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረ ብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ተከብሯል። እንደምታውቂው የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በቅርብ ዓመታት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተለይተው ከተዋቀሩ ሁለቱ ክልሎች አንዱ ነው። ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ቀጥሎ ከብዙ ውዝግብ በኋላ ክልል ሆኖ የተዋቀረ ነው።
የጉራጌ ዞንን ጨምሮ በርካታ ዞኖች ራሳቸውን ችለው ክልል ለመሆን ብርቱ ጥያቄ ሲያቀርቡ ነበር። ጥያቄው ወደ አመጽ ያመራበትንአጋጣሚ ሁሉ እናስታውሳለን። አሁን ግን ክልሉ አንጻራዊ መረጋጋት አሳይቶ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከምታከብራቸው መንግስታዊ በዓላት አንዱን ዛሬ ሆሳዕና አስተናግዳለች።
በመንግስት የመገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ስርጭት እንደተመለከትነው በሀገሪቱ የኮሪደር ልማቶች ሆሳዕናንም እንዳሰመራት ተመልክተናል። በ,ርግጥ ነው ፤ ሆሳዕና ቀድሞም ቢሆን ስሟ በስደት ደቡብአፍሪቃ ከሚኖሩ የሃዲያ ብሔር ተወላጆች ኢንቨስትመንት ጋር ተደጋግሞ ሲነሳ ይሰማል። አሁን ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ለውጥ እንዳሳየችም መረዳት ይቻላል። የሆነ ሆኖ ዛሬ በተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ላይ በቅድሚያ ንግግr ያደረጉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ናቸው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የሃዲያ ህዝብን አመስግነዋል
ጠቅላይ ሚንስትሩ የበዓሉ አስተናጋጅ የሆነውን የሃዲያ ህዝብ በማመስገን ነው ንግግራቸውን የጀመሩት ። ጠቅላይ ሚንስትሩ ምስጋናቸውን የጀመሩበት ሃሳብ ከኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስን በማስታወስ እና ወጣቶችን በማነሳሳት ነበር ። ኮሌኔሉ የጀመሩትን ወጣቶች ትጨርሳላችሁ በማለት ነበር።
ጠቅላይ ሚንስትር አቢይ አህመድ ያደረጉት እና ትኩረት ያገኘው ሌላው ሃሳብ ደግሞ ሰይጣናዊ ያሏቸውን ተግባራት ሁሉ አሸንፋ ኢትዮጵያ እንደምትበልጽግ እና ጠላቶቻችን ያሏቸውን ደግሞ እንደ ጸጉር ቅማል እንለቃቅማቸዋለን ብለው የገለጹበት ሃሳብ አንዱ እና ምናልባትም አነጋጋሪው ሳይሆን አይቀርም
ጠቅላይ ሚንስትሩ በንግግራቸው ዛሬ ከተሞቻችን እያሸበረቁ ገጠር መንደሮቻችን ለመሻገር ደፋ ቀና እያሉ፣ ታሪካዊ ቅርሶቻችን አቧራቸውን አራግፈው የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ኩራት መሆናቸውን በገሃድ እያሳዩ ናቸው» ብለዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ንግግር
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣ ስለሃገራዊ የምክክር መድረክ ስኬታማነት እና መንግስት ለመጭው ሃገራዊ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በዕለቱ ንግግር ካደረጉት ውስጥ ለየት ያለ ሃሳብ ይዘው ብቅ ያሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንዳሻው ጣሰ,ው ናቸው። ርዕሰ መስተዳድሩ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ህዝብ የባሕር በር ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ከመንግሥት ጎን በመቆም የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ ነው » ብለዋል። ይህ ጥሪ ቀደም ሲል ጠ,ቅላይ ሚንስትሩ ከኮሎኔል በዛብህ ጴጥሮስ ጋር አያይጠው ላስተላለፉት መልዕክት ማጠናከሪያ ሳይሆን አይቀርም ።
የተለያዩ መልዕክቶች የተላለፉበት እና በርካታ ኩነቶችን ያስተናገደው የበዓሉ ስነስረዓት ሲጠናቀቅ ደቡብ ምዕራባዊቷን የኦሮሚያ ክልል ከተማ ጅማን የ21ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀንን እንድታከብር በመምረጥ ተጠናቋል። የጅማ ከተማ ከአዲስ አበባ ከተማ በስተ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በ353 ኪሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።
የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን የባለስልጣናቱን ንግግር ያድምጡ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ























